9

«በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፤ ወደ እኔም እንዳመጣችሁ አይታችኋል!»

ንስር ንጉሠ አዕዋፍ ነው፤ በመብረርም ፈጣንና ጠንካራ የሆነ ነው፡፡ ረዥም ዘመን የሚኖር፣ ከሩቅ አጥርቶ የሚያይ፣ እስከ ተራሮች ከፍታና ከደመናት በላይ ለመብረር የሚያስችሉ ኃያላን አክናፍ ያሉት ነው፡፡ እንዲሁም ንስር ለጫጩቶቹ ርኅሩኅ ነው፡፡ በጥበብ ይንከባከባቸዋል ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙም ያለማምዳቸዋል፡፡

ከእነዚህ ተነጻጻሪ ባሕርያት የተነሣ እግዚአብሔር በትሕትና ራሱን ከንስር ጋር አመሳስሏል፡፡ እግዚአብሔር ዘላለማዊ፣ ሁሉን ቻይ፣ ሁሉን ተመልካች (ሁሉን የሚያይና የሚያውቅ የጥበብ ምንጭ)፣ ምሕረትን የተሞላ፣ ለሕዝቡ የሚራራና ወደ ድኅነት የሚመራቸው ነው፡፡

ጌታ እግዚአብሔር ሕዝቡን መርቶ ከግብፅ ባወጣቸውና ከፈርኦን ሠራዊት ጠብቆ በተአምር ቀይ ባሕርን ባሻገራቸው ጊዜ እንዲህ ብሏቸው ነበር፡- ‹‹በግብፃውያን ያደረግሁትን በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል›› (ዘጸ. 19፥4)፡፡

በንስር ሕይወት ውስጥ ካሉት ምሥጢራት አንዱ ሁልጊዜ ጎጆውን በከፍታ ላይ መሥራቱና በአለታማ ቋጥኞችና ምሽጎች ውስጥ መኖሩ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለኢዮብ ጥበቡንና ኃይሉን ሲያሳየው ያለውን ልብ በሉ፤ ‹‹በአፍህ ትእዛዝ ንስር ከፍ ከፍ ይላልን? ቤቱንስ በአርያም ላይ ያደርጋልን? በገደል ላይ ይኖራል፤ በገደሉ ገመገምና በጥጉ ያድራል፡፡ በዚያም ሆኖ የሚነጥቀውን ይጎበኛል፤ ዓይኑም በሩቅ ትመለከታለች፡፡›› (ኢዮ.39፥27)

ንስር ስለምን ከፍ ብሎ ጎጆውን በተራሮች ጫፍ ላይ ይሠራል?

እንደ አዳኞችና አራዊት ያሉ ጠላቶቹ ሊደርሱበት ከማይችሉበት ስፍራ ለመገኘት ብሎ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ወደ ጎጆው ደርሶ ጫጩቶቹን ሊበላበት የሚችል ሌላ ጠላት አለ፡፡ ይህም ጠላት እስከዚያ ከፍታ ድረስ እስኪደርስ በልቡ ሊሳብ የሚችለው ዕባብ ነው፡፡

ታዲያ ይህንን ውስብስብ ችግር ንስር እንዴት ይፈታዋል?

ዕባቡ ዘልቆ እንዳይገባ ጎጆውን በመጠን ብዙ በሆኑ እሾኆች ከውጪ በኩል ያጥረዋል፡፡ የጎጆው ውስጠኛ ክፍል ደግሞ በላባዎች የተደራጀ ሞቃታማና ምቹ ነው፡፡ ውጪው ግን በእሾኽ የታጠረ ነው፡፡ ታላቁ ንስር ለጫጩቶቹ ጥሩ እንክብካቤ ያደርጋል፡፡ የሚበሉትን ያቀርብላቸዋል፤ በክንፎቹ እያንዣበበ ይጋርዳቸዋል፤ በአፉ (በመንቆሩ) ይመግባቸዋል፡፡ ትንንሾቹ አንስርት (ንስሮች) እንዳሻቸው እንዲኖሩ የተተዉ ቢሆኑ ኖሮ ለዘላለም ከጎጆአቸው ባልወጡ ነበር፡፡

ስለዚህ ጊዜው ደርሶ ጫጩቶቹ ሲያድጉ ታላቁ ንስር የመብረር ችሎታቸውን ይፈትናል፤ ጎጆውንም መትቶ ያነቃንቀዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ መገፋቱ ጠንከር ሲል ጎጆው ከተራራው ጫፍ ወደ ዝቅተኛው ጫፍ ሊወድቅ ይችላል፡፡

ጎጆው በተነዋወጸ ጊዜ ከውጪ ያሉት እሾኾች ወደ ውስጥ ይገባሉ፤ በጫጩቶቹም ላይ መወጋትንና ሕመምን ያስከትላሉ፡፡ ክንፎቻቸውን ያንቀሳቅሳሉ ለመብረርም ይሞክራሉ፡፡ ከተሳካላቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ለመብረርና ንጹሑን የሰማይ አየር እየተነፈሱ ለመደሰት ይችላሉ፤ ዳግመኛም ወደ ጎጆአቸው በፍጹም አይመለሱም፡፡ በዚህም ተልእኮውን በሚገባ ያለችግር በማከናወኑ ታላቁ ንስር ደስታ ይሰማዋል፡፡

የጫጩቶቹ የክንፋቸው ላባ በበቂ ሁኔታ ካላደገና መብረር ሳይቻላቸው ከወደቁ ታላቁ ንስር ፈጥኖ ክንፎቹን ዘርግቶ ይይዛቸዋል፤ በክንፎቹም ይሸከማቸዋል፡፡ ለተጨማሪ ቆይታም ወደ ጎጆአቸው ይመልሳቸዋል፡፡ ይህንን ዑደት መብረር እስከሚችሉ ድረስ ይደጋግመዋል፡፡ አይደንቅም ትላላችሁ?

‹‹ንስር ጫጩቶቹን እንደሚያወጣ በእነርሱም ላይ እንደሚሰፍፍ ክንፎቹን ዘርግቶ ወሰዳቸው፤ በክንፎቹ አዘላቸው፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን ብቻውን መራው›› ዘዳ.33፥10

ከላይ እንደተገለጠው እግዚአብሔር ራሱን ከንስር ጋር አመሳስሏል፡፡ እኛም ከድንቅ ፍጥረቱ ከንስር ሕይወት አንዳንድ ቁም ነገሮችን እንቀስማለን፡፡

ምእመናን የንስር ጫጩቶችን ይመስላሉ!

የንስር ጫጩቶች ደካሞችና በራሳቸው ለመቆምና በራሳቸው ለመኖር የማይችሉ ናቸው፡፡ የሰው ልጅም ሲወለድ በራሱ መብላት መጠጣት፣ መሄድ፣ መናገር፣ ማሰብ፣ ፍላጎቶቹን መፈጸም የማይችል ሆኖ ነው የሚወለደው፡፡ በተመሳሳይ በመንፈሳዊ ሕይወቱም ጠላቶቹን፣ ኃጢአትን፣ ሰይጣንን፣ የሥጋ ምኞትንና የዚህችን ዓለም መስህብነት ለመቃወም ደካማ ነው፡፡

ነቢዩ ንጉሥ ዳዊት ይህንን እውነታ ከአስከፊው ውድቀቱ በኋላ በስድስተኛው መዝሙሩ ሲገልጥ ‹‹አቤቱ በቊጣህ አትቅሠፈኝ በመዓትህም አትገሥጸኝ፡፡ ድዉይ ነኝና አቤቱ ማረኝ›› ብሏል፡፡ (መዝ.6፥1-2) የእግዚአብሔር ንቁ ዓይኖች፣ ኃያላን ክንዶቹና ሁልጊዜ በላያችን የሚጋርዱን ክንፎቹ ያስፈልጉናል፡፡ ይህንን ደካማነታችንንና ኃጢአተኛነታችንን እስካላመንን ድረስ ግን የእግዚአብሔር ኃይል ወደ እኛ ፈጽሞ አትመጣም፡፡

በሌላ ያማሩ ቃላት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በሰማያት ላይ ለረድኤትህ በደመናትም ላይ በታላቅነት እንደሚሄድ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም፡፡ መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው ፤ የዘላለም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፡፡››
(ዘዳ.33፥26)
የንስር ጫጩቶች እንደ እኛ አላዋቂዎች ናቸው፡፡ እኛ ከትምህርታችንና ከዲግሪዎቻችን ያገኘነው ምንም ይሁን ምን አላዋቂነታችንንና የእግዚአብሔር መሪነት እንደሚያስፈልገን ማመን ይገባናል፡፡ በመንፈሳዊው ዕይታ የሰው ልጅ አላዋቂ ነው፡፡ ወደፊት ስለሚመጣው ነገር፣ ከሞት በኋላም ስላለው ነገር፣ ሌላው ቀርቶ ስለ ራሱና በፍጥረታት ውስጥ ስላሉ በሚልዮኖች ስለሚቆጠሩ ነገሮች እንኳን አያውቅም፡፡ ማየት የማይችል ከመሆኑም የተነሣ የቃለ እግዚአብሔርና የመንፈስ ቅዱስ ብርሃንነት እንዲሁም ምክረ ካህን ያስፈልገዋል፡፡

እግዚአብሔር እኛን የሚንከባከብበት መንገድ ከንስር ጋር ይመሳሰላል!

ንስር ከፍ ከፍ እንደሚልና ጎጆውን በከፍታ ላይ እንደሚሠራ እግዚአብሔርም ልጆቹ ከሌላው ሰው በተለየ መዓርግ እንድንኖር ይፈልጋል፡፡ በቅድስና ሕይወት እንድንኖርና ከእርሱ ጋር ለዘላለም በመንግሥቱ ለመኖር ራሳችንን እንድናዘጋጅ ይፈልጋል፡፡ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ በጥምቀት ከተወለድን ጀምሮ የመንግሥተ ሰማያት ዜጎች ሆነናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 3፥20፡ ‹‹እኛ ሀገራችን በሰማይ ነውና›› ብሏል፡፡ ከሰማያዊው አምላክ ተወልደናል፤ ምግባችን ቃለ እግዚአብሔርም፣ ሥጋ ወደሙም፣ ጸሎትና አንድነታችንም ሁሉም ከላይ ነው፡፡ ‹‹በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፤ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ›› (ያዕ.1፥18)፡፡

ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም፡፡ ሞታችኋልና ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ›› (ቈላ. 3፥1-4)፡፡

እግዚአብሔር ጎጆአችንን በእሾኾች ያጥረዋል!

በእርግጥ እግዚአብሔር ጥቂት እሾኾች እንዲያቆስሉን ያደርጋል፤ ይህም ፍቅሩንና ለእኛ ማሰቡን የሚያስረዳ ነው፡፡ በእሾኽ እንድንወጋ የሚፈቅደው በቁስላችን፣ በስቃያችንና በሕመማችን ስለሚደሰት አይደለም፤ በዚህ ስቃይ እንድናድግና እንድንጎለምስ ሊያስተምረንና ሊያለማምደን ነው እንጂ፡፡ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ስቃይና መከራ አልቀረለትም፤ እንዲያው በተገላቢጦሹ እስከ መጨረሻው መራራ ጽዋን ጠጣ፡፡ እንዲህ ተብሎ ስለ እርሱ እንደተጻፈ፡- ‹‹ምንም ልጅ ቢሆን ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ (ዕብ. 5፥8)››

ሌሎችን የመፈወስ ጸጋ የተሰጠው ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ ‹‹በሥጋው ላይ ስለነበረበት እሾኽ›› አቤቱታ አሰምቶ ነበር፡፡ እንዲህ ማለቱን ልብ በሉ፡ ‹‹ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መውጊያ ተሰጠኝ ይኸውም እንዳልታበይ ነው፡፡ ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ፡፡ እርሱም ፡- ጸጋዬ ይበቃሃል ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ፡፡ እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ፡፡ ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና›› (2ቆሮ. 12፥7-10)፡፡

‹‹ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው፡፡ ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና (ሮሜ. 8፥20-22)››

ስለዚህ እግዚአብሔር በእነዚህ እሾኾች እኛን በማሰቃየት ደስታን የሚያገኝ ሆኖ አይደለም፤ ይህ ለድኅነታችን አስፈላጊና ወሳኝ የሆነ ልንሸከመው የሚገባን መስቀል ስለሆነ ነው፡፡ ንስር ልጆቹን ከዕባብ ለመጠበቅ ጎጆውን በእሾኽ እንደሚያጥር እግዚአብሔርም ከቀደመው ዕባብ ከዲያብሎስ እጅ ይጠብቀን ዘንድ በሕይወታችን ውስጥ ጥቂት እሾኾች እንዲኖሩ ይፈቅዳል፡፡ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን ‹‹ለምን?›› ብለን እንጠይቀዋለን፡፡ እርሱም እንዲህ ሲል ይመልሳል፡- ‹‹እኔ የማደርገውን እናንተ አሁን አታውቁም በኋላ ግን ታስተውሉታላችሁ›› (ዮሐ.13፥7፣ መዝ. 72፣ ዕብ.12)፡፡

ንስር ጎጆውን እንደሚያናውጽ እግዚአብሔርም እንዲሁ ያደርጋል!

እሾኾች ጫጩቶቹን ለመብረር እንዲገፋፉ ለማድረግ ሲል ንስር ጎጆውን ያነዋውጻል፡፡ ይህ ዓይነተኛ ፈተናና ትምህርት ነው፡፡ በእኛም እንዲሁ ነው፤ እግዚአብሔር ጎጆአችንን በኃይል ያነዋውጸዋል፤ ይሁናና በፍጹም አያፈርሰውም፡፡

ይህ ንውጽውጽታ ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሣ ሊያስደነግጥ ይችላል፤ ይሁንና አትጨነቁ ዓላማውንም አትዘንጉ፡፡ እንድትበርሩ ሊያስገድዳችሁ ነው፤ አዎን በሰማያዊው ህዋ ደስ እንድትሰኙ ሊያደርግ ነው፡፡ በዘመናችን የሚከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥና ዓውሎ ነፋስም የብዙዎችን ጎጆ የሚያናውጽና ሰዎችን ለንስሓ ለማዘጋጀት የሚደረግ የማንቂያ ጥሪ አንዳች ማሳያ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በመንግሥቱ ለዘላለም የምንኖርበትን ዘላለማዊ ጎጆ አዘጋጅቶልናል፡፡ ስለዚህም ሰነፎችና ከዚህች ዓለም ጋር የተሳሰርን እንድንሆን አይፈልግም፡፡ ይህን ታላቅ ተስፋ በልባችሁ አኑሩ፤ ምድራዊ ስቃይን ሁሉ ትዘነጋላችሁ፡፡ ‹‹የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ›› በእናንተ ዘንድ እንዳለም አስታውሱ (ቈላ. 1፥27.)፡፡ ከዚህ ተግባር ጠቀሜታዎች አንዱ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔርን በመተማመን መጠባበቅንና ኃይልን ማደስን እንደ ንስር በክንፍ መውጣትን›› የምንማር መሆናችን ነው (ኢሳ. 40፥31)፡፡ እርሱ ‹‹መንግሥትህ ትምጣ›› ብለን እንድንጸልይ አስተምሮናል፡፡ እናም አንድ ቀን ወደ ሰማይ እንነጠቃለን፤ ወደ ምድራዊው ጎጆአችንም በፍጹም አንመለስም፡፡

ክንፎቹን ዘርግቶ ይሸከማቸዋል!

መዝሙር 90 ይህንን እውነታ በሰፊው ያስረዳል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ፈጣን እርዳታ፣ ስለ መግቦቱ፣ ጥበቃውና አድኅኖቱ ይናገራል፡፡

‹‹በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል፡፡ … እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና፡፡ በላባዎቹም ይጋርድሃል፤ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፤ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል›› /መዝ. 90፥1-5/፡፡

ቀሲስ አውግስጢኖስ ሀና /ግብፃዊ/
ትርጉም ፡ ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ST. JHON / Monthly Magazine of Coptic Orthodox Church.
Vol. 17 no. 190 November 2005

Share this:

Like this:

Like Loading...

Discover more from በኢ/ኦ/ተ ሐመረ ኖኀ ኪዳነምህረት ወቅዱስ ሚካኤል ወአቡነ ተክለሃይማኖት ካቴድራል ላስ ቬጋስ

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading