Poem
አብነቱ ማንነቱ ፤ ማንነቱ አብነቱ
ድጓ ቅኔ ዜማ ጥበብ
መፍለቂያዋ ሆነሽ ድባብ
ስታፊሪ ሀገር ስትከብር
ስመ ጥሩ ጠቢብ ምሁር ካንቺ ወጥቶ ካንቺ ተምሮ
በእውነት ዳብሮ በእውቀት ከብሮ
ካንቺ ተገኝቶ በአባቶች እግር ተተክቶ
ሃይማኖት ባህል ወግሽ
ሥርዓትና አብሮ መብላትሽ
እንቁ ሆኖ እያበራ
ሀገር ስሟ ባንቺ ሲጠራ
ተነጥላ ኢትዮጵያችን ከሃይማኖቷ
ሀገር ላትሆን ተሳሥራለች በትውፊቷ
ቅኔ ዜማ ዘመን ቆጥረው ለሳይንሱ መንገድ ቀደው
መንገድ ከፍተው
ንጉሥ ሀገር የሚመራ
ካንቺው መንደር ካንቺ ጐራ
ወጥቶ ታየ ጥሩ አዝመራ
ሕግ አዋቂ አማካሪ
ፕሮፌሰር ተመራማሪ
ያፈራሽ ንጹሕ መሬት
ሳትግዢ በቅኝ ግዛት
እንድትኖሪ በእኩልነት በነፃነት
ምን ተገኘ ምን መጣና
ምንጭሽ ይድረቅ ተባለና
እንዲነጥፍ አገልግሎት
እንዳይፈሩ አበው ሊቃውንት
እንድትጠፊ ከገጸ ምድር
አሴሩብሽ እኩይ ግብር
ሃምሣ ሎሚ ላንድ ሽክሙ ለሃምሣ ጌጡ
አበው አሉ መረዳዳት መካፈልን ሲገልጡ
በሉ እናንተም ካላችሁ ላይ ለአብነቱ ጥቂት ስጡ
ነቅና ጉድፍ ከሌለበት
ዘር እንዲገኝ ከአብነት
የአፍሪካ ቀንድ የጥቁር ሕዝብ መመኪያቸው
የሚያከብሩሽ የሚመኩብሽ ምሳሌያቸው
ለምን ይንጠፍ ይድረቅ ምንጭሽ
ይኼ ሁሉ ልጅ እያለሽ
የታሪክ ምንጭ የቅርስ እመቤት
ለዓለም ሕዝብ ሻማ መብራት
እንደ ላቲን አሜሪካ
በአሕጉራችን በአፍሪካ
አልቦ ታሪክ እንደሆኑት
በቅኝ ግዛት እንደጠፉት
ቅርስ አልባ አትሁን ሀገራችን
ምንጯ ይፍሰሰ በምድራችን
ቅኔ ቆጥረው ቅሬ ዘርፈው
አኩፋዳ ቅምጫና ይዘው
ተማሪዎችሽ ፍርፋሪ ቁራሽ አጥተው
ከውሻ ጋር ትግል ገጥመው
ያቆዩልን በቁስል በደም በሞታቸው
አይዘጋ አይታጠፍ ወንበሩ
የታላቁ ሰው የመምህሩ
ቀለም ብዕር ብራናውን አዘጋጅተሽ
አንቺው ቀርጸሽ አንቺው ድጠሽ
አሐዝ ቀርጸሽ ቃላት ጽፈሽ
ለአዲስ ትውልድ አስተላልፈሽ
አመሥጥረሽ አስተምረሽ ብሉይ ከሐዲስ
ማርይስሐቅ አረጋዊ መንፈሳዊ ፊሊከሰዩስ
ሥርዓትሽ ፍትሐ ነገሥት ዲድስቅልያ
ያቆየሽዉ ምንጩ አንቺነሽ አቅሌስያ
ዘአምላኪየ ጉባኤ ቃና ቅኔ ዘርፈሽ
ሥዕላቱ እንዲነበቡ መልክ ሰጥተሽ
ታሪክ ገልጠሽ ቅርስ አኑረሽ
ለትውልዱ እንዲቆየው
ማንነቱን እንዲረዳ እንዲለየው
አትንጠፊ አትድረቂ እንዳይቆጨው
ሕግ ፍትሕ አስተዳደር
እንዲሠራ በዚች ምድር
ፈር የቀደድሽ የከፈትሽ በር
ቀን ቆጥረሽ ዘመን ቀምረሽ
ለዓለም ሕዝብ ባስተዋውቅሽ
ወንበር አጥፈው መምህራንሽ
ለምን ይበተኑ ይሰደዱ ተማሪዎችሽ
በቅኝ ገዢዎች ሴራ ገብተው
ያንቺው ልጆች ያንቺው ማኀፀን ያፈራቸው
አብነቱ እንዲጠፋ
ዘረኝነት እንዲሰፋፋ
እንዲዘረፍ ሀብትሽ ቅርስሽ
አስተዋጽኦ አረጉብሽ
ልጆቻችን ከእኛ ወጥተው
ባህል ወጉን ሁሉን አጥተው
ባእድ ሆነው ባዕድ መስለው
በቤታቸው ባገራቸው
በምንጫቸው በወንዛቸው
ጨከኑባት ሳይገባቸው
አዘኑለት ለነገው ሰው
ያለታሪክ ማንነቱን ለማያውቀው
ነበር እንጂ አለ ተብሎ ላይታየው
ከቶ አይጥፋ አይደምሰስ መለያው
ካልበረታን ካልተባበርን
አብነቱን ካልገነባን
አቤት የነገው እጣ ሲዘገንን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
by: Martha Shita
