ዳዊት በቅንአት ተነሳስቶ
እንደዚህ አለው ናታንን ጠርቶ
እኔ ባማረ በዝግባ ቤት
ደስታዬን ስገልጽ በሰገነት
የእግዚአብሔር ታቦቱ እንዴት ይቀመጥ መጽ. ሳሙ ካልዕ 7 ፤ 2
በመጋረጃ በድንኳን ውስጥ
እግዚአብሔርም አለው መለሠና
ዳዊትን ቅንአቱ አየውና
የእሥራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር
ካወጣሁ ጀምሮ እኔ ማድረ
በድንኳን እንጂ ቤት መች ኖረኝ
አሁንም አንተ አትሠራልኝ
ዳዊትም ልጁ ሰሎሞንን መጽ. ዜና መዋዕል ቁ 22፤4
ጠርቶ ነገረው መልካም ቃልን
ለእግዚአብሔር ቤትን እሠራ ዘንድ
በልቤ አስቤ ሳወጣ ሳወርድ
ወደ እኔ መጣ ቃል ከእግዚአብሔር
ዳዊት አድምጠኝ ይህን ነገር
ታላቅ ሰልፍ አርገህ ነበርና
እጅህ ደም በፊቴ አፍሷልና
ስለዚህ ቤቴን አንተ አትሠራም
እጆችህ ከሰው ደም አልጠሩም
የእረፍት ሰው የሚሆን ልጅ 1ሳሙ. 7፤2- ፍ
ካንተ ይወለዳል ለእኔ የሚበጅ
ሰላም ፀጥታን ለእሥራኤል
እመልሳለሁ አለ የአምላክ ቃል
እድሜህ ሲፈፀም አንተ ስታልፍ
ብዙ ሠራዊት በማሰለፍ
ስታንቀላፋ እንደአባቶችህ
የሚወጣው ዘር ከወገብህ
እኔ በጊዜው አስነሳና
መንግሥት ዙፋኑን አጸናና
ሰሎሞን ልጅህ ማደሪያዬን
ቤቴን ይሠራል አንተ አትዘን
ብሎ ነገረው የተስፋ ቃል
የሚሆነውን አምላክ ያውቃል
ኋላም ዘመኑ ቀኑ ሲደርስ
ግሩም የሆነ ቤተ መቅደስ
በብርና ወርቅ የተጌጠ
በእግዚአብሔር ፈቃድ ተገለጠ
ዛሬም በሰዶም በጐሞራ
እግዚአብሔር አምላክ ድንቅን ሠራ
በቀራንዮ ጐልጐታ
በእኛ ኃጥያት ሲሰቀል ጌታ
ጐኑን ሲወጋ በጦር
ክቡር ደሙ ፈሶ ነበር
ኡራኤል ረጨው መላ ዓለሙን
በእሳት ጽዋ ቀድቶ ደሙን
ደሙ ሲረጭ ያኔ ገና
ላስቬጋስ ላይ ነጠበና
ፈቃዱ ሲሆን ጊዜው ሲደርስ
ተሰርቶ አየን ቤተ መቅደስ
እጽብ ድንቅ ነው የአምላክ ሥራ
ጥንትም ዛሬም ከእኛው ጋር
እጅግ ኃጥያት ባለበት ሥፍራ
ፀጋው በዝቶ ተአምር ተሠራ
በእውነት ህልማችን እውን ሆነና
አየን መቅደሱን ገነባና
እንደበት ኖሮት ቢመሰክር
ላስቬጋስ ያለ ቤተመዘክር
በመናፈሻ በሠው ቤት
እንባችን ሲፈስ በታላቅ ጮኸት
ይሠማል ጆሮን የፈጠረ
አንድ ሁለት ብሎ ቀን ቆጠረ
ፀሎት ዋጋዋን አላጣችም
አንኳኩታ ደርሳ ከመድህን ዓለም
ህልማችን ሁሉ እውን ሆነና
አየን መቅደሱን ገነባና
ጽላት ማረፊያ አጥቶ ሲመላለስ
ሥፍራ ሳይኖረው መንበር መቅደስ
ለብዙ ዓመታት ሲንከራተት
ይመስገን አምላክ ቀን ሞላለት
በእውነት ህልማችን እውን ሆነና
አየን መቅደሱን ገነባና
አንተን ለማምለክ ለማመስገን
ሽሽት ሆኖብን ሌትና ቀን
ካንዱ ስንወጣ ሲያሳድዱን
ማረፊያ ማግኘት ግድ ሲለን
ጠላት ዲያብሎስ ቀስቱን ተክሎ
በሠው ልቦና መርዙን ጥሎ ፍቅር አቅዝቅዞ ጠብ አንግሶ
ጥቂቱን አግዝፎ አባብሶ
ጠብ ዘርቶ አንዱን ካንዱ አናክሶ
ኩርፊያን ደርቦ ካባ አድርጐ
ልብን በክፋት አዝጐ
በስደት ሳለን በሠው ሀገር
አንዱን ከሌለው ሲያናቁር
ሊነግስ አስቦ በዚህች ሥፍራ
እቅዱ ሁሉ ሆኖ ተራ
ለራት አይበቃም ልጅ ያቦካው
ነገ ይፈርሳል ሕብረታቸው
ነበር በጊዜው ተረታቸው
እግዚአብሔር ይክበር ሁሉ አለፈ
የሠይጣን ሴራው ደርቆ ረገፈ
በእውነት ህልማችን እውን ሆነና
አየን መቅደሱን ገነባና!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
By: Marta Shita
